Cart

No products in the cart.

Blog

  • Home
  • History
  • ,
  • Media

መዝገቡ አባተ፣ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘሪሁን:-መጽሐፍ በሊታዎች

መዝገቡ አባተ፣ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘሪሁን:-መጽሐፍ በሊታዎች

መዝገቡ አባተ፣ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘሪሁን:-መጽሐፍ በሊታዎች (Book worms)፣ መጻሕፍት አዳኞች(book hunters)

እና የቤተ-መጻሕፍት/የቤተ-ፍርግም ፈታሾች(library hunters)

ከጌታቸው ወልዩ
—————————-///—————————–
በዘመን ተሻጋሪ ጽሑፎቻቸው/የድርሰት ሥራዎቻቸው የብዙ ሺ አንባብያንን ቀልብና ስሜት በመግዛታቸው ብዙዎች የእዝነ-ልቡናቸውን በር ከፍተው እንደ ተወዳጅ ቤተኛ ሁነኛ ቦታ የሰጧቸው፤ በበሳል ብዕር ትሩፈቶቻቸው ጣዕም ልኬት የተነሳ ምሁራንን ጨምሮ ለንባብና ለመገናኛ ብዙሐን የቀረቡ አያሌ ወገኖች በአእምሯቸው ጓዳዎች ቁልፍ ቦታ የቸሯቸው፤ ከፍ ባለው የሥነ-ጽሑፍ አቅማቸው ስማቸው በኢትዮጵያ ታላላቅ ደራስያን የክብር መዝገብ ውስጥ በአክብሮት የተጻፈላቸው ናቸው:-በድርሰትና ጋዜጠኝነት ሙያ ዘርፎች ለረዥም አመታት ያገለገሉት፤ የስመ-ጥርነት/የታዋቂነት ካባ ደጋግመው ለመደረብ የበቁት- መዝገቡ አባተ፣ ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘሪሁን።
መዝገቡ አባተ፣ ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘሪሁን፦ ጥንታዊ/የቆዩ/አሮጌ መጻሕፍትን ጨምሮ አዳዲሶቹን መጻሕፍት ከግለሰቦች ከመዋስ አንስተው፤ ከመጻሕፍት መሸጫዎች እስከ ቤተ-መጻሕፍት ማከማቻ (አርካይቭስ) ዘልቀው እያፈላለጉ በማንበባቸው፤ የዚያን ዘመኑ (1950ና 60ዎቹ) ሹመኞችን ጨምሮ ምሁራን፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸውና አንባቢነታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ወገኖች የመጻሕፍት አዳኞች (book hunters) እና የቤተ-መጻሕፍት/የቤተ-ፍርግም ፈታሾች (library hunters) ይሏቸው ነበር፤ የንባብ ክኅሎታቸውን በማድነቅና በማክበር።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስከ ዘመናችንም ድረስ፤ “የመልካም ስም ፈረስ ዘወትር ወደፊት ይገሰግስ!” እንዲሉ፤ በእጆቻቸው የገቡ መጻሕፍትን፣ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ከዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴያቸው ጋር አድርገው፤ አንድን ጽሑፍ ከጫፍ እስከ ጫፍ፤ ከጅማሬ/መነሻ እስከ ማጠቃለያ/መዳረሻ በጥልቀት በማንበባቸው፤ “የመጽሐፍ በሊታዎች” (Book worms) ነበር/ነውም የንባብ ተቀጥላ ስማቸው፤ በብዙ ባልንጀራዎቻቸውና አድናቂዎቻቸው።
እንደሚታወቀው መዝገቡ አባተ፣ ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘሪሁን በርካታ የታሪካዊ መጻሕፍት ስብስብ የነበራቸው፤ በዋናነት የኢትዮጵያ ታሪክ ቀልባቸውን የወሰደባቸው፤ ስለኢትዮጵያ ነገሥታትና ስለኢትዮጵያ ታሪክ የጻፉ፤ በዘመናቸው በታሪክ ድርሰት፣ በታሪክ ነጋሪትና ተመራማሪነት ከቀዳሚዎቹ ኢትዮጵያውያን ፀሓፍት ጋር አብረው ከፊት የተሰለፉ፤ ደራስያንና ጋዜጠኞች ናቸው፤ የድርሰት ሥራዎቻቸው ስማቸውንና ሙያቸውን ያገዘፉላቸው።
ለአብነት ያህል:-የመዝገቡ አባተን “ጠቅል አብነቴ ፍጹም መድኃኒቴ”፣ “ጠቅልነህ መኩሪያችን መከበሪያችን” እና ከረዥም አመታት በኋላ በቅርቡ የታተመውን “ኢትዮጵያ መልክዓ-ምድሯ፣ ሕዝቦቿ፣ አስተዳደሯና ኢኮኖሚዋ” መጻሕፍቱን መጥቀስ እንችላለን፤ የመዝገቡን መጻሕፍት እንደ ታሪክ የትውስታ ባቡር ተጠቅመን የቀዳማዊ ኃይለ-ሥላሴ ዘመንን ዛሬ ላይ ቆመን እየቃኘን።
ጳውሎስ ኞኞ በበኩሉ፦ “የኢትዮጵያ ታሪክ ኢንሳይክሎፒዲያ”፣ “የአጤ ቴዎድሮስ ታሪክ”፣ “የአጤ ዮሐንስ ታሪክ” “የአጤ ምኒልክ ታሪክ”፣ “አጤ ምኒልክ ከውጭ ሀገራት ጋር የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች”፣ “የኢትዮጵያና የጣልያን ጦርነት” በማለት፤ ቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታትና የኢትዮጵያን ታሪኮች በበሳል ብዕሩ ጽፎ ለትውልድ አሸጋገረ፤ የታሪክ እውቀት ክምችቱን በታሪክ መጻሕፍቱ ውስጥ በአግባቡ ቀንብቦ ወገንን እያስተማረ።
ኋላ ላይ “ባልቻ አባነፍሶን” ተውኔት የጻፈው ብርሃኑ ዘሪሁን፤ በደብተራ ዘነብ “መጽሐፈ-ጨዋታ ሥጋዊ ወ መንፈሳዊ” ጽሑፍ እጅጉን ስሜቱ ተስቦ፤ ስለ አጼ ቴዎድሮስ (የቋራው ካሳ) የሥልጣን መወጣጫ ጉዞ፣ ኢትዮጵያዊነት የከፍታ ዕይታና የመቅደላ ዓምባ ፍጻሜያቸውን “በቴዎድሮስ ዕንባ” መጽሐፉ ከትቦ፤ “በታንጉት ምስጢር” መጽሐፉ የአጼ ቴዎድሮስን ኀያሉን የጦር ሹመኛ ፊታውራሪ (ጄነራል) ገብርዬ ጎሹንና የአጼ ቴዎድሮስ የቅርብ ዘመድ ታንጉትን የፍቅር ተራራ ላይ አውጥቶ የፍቅር ቡልኮ አስደርቦ፤ ድርሰትን እንደ ንቁ ታታሪ ገበሬ ማሳ አበጃጅቷል፤ በዚህም የሥነ-ጽሑፍ አዝመራው ፍሬ ያማረ መሆኑን አመላክቷል።
ሙያቸውን በትጋት፣ በጥረትና ፍላጎት ያጀቡት ሦስቱም ደራስያንና ጋዜጠኞች በዘመናቸው የሕዝብ ቃፊር በመሆን የድፍረትን ካባ ተከናንበው በጻፏቸው የድርሰት ሥራዎችም የሚታወቁ ናቸው፤ ለበርካታ የቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ተማሪዎችና ምሁራን፣ ደራስያንና ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶችን ጨምሮ ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች አርአያ (ተምሳሌት) በመሆናቸው።
ለመጥቀስ ያህል መዝገቡ አባተ በሥልጣናቸው የባለጉና ለሕዝብ ጥቅም ያልተጉ ባለሥልጣናትን (ሹመኞችን) “ዋ መጨረሻቸው!” በሚል ርዕስ ባሰናዳው መጽሐፉ ተችቷቸዋል። ሳንሱር የጎበኘው ረቂቅ መጽሐፉም የኅትመት ብርሃን ተነፍጎታል።
ጳውሎስ ኞኞም የሐሙሷ ሳምንታዊ “አዲስ ድምጽ ጋዜጣን” ይበልጥ ተነባቢና ተወዳጅ ባደረገበት ዘዴው፤ ጋዜጣ አዟሪዎችን አረንጓዴ የደንብ ልብስ አልብሶ ማስታወቂያ በማሠራቱ፤ የማስታወቂያና መርሐ-ብሔር ሚኒስትሩ ግርማቸው ተክለ-ሐዋርያትን ተከፍተው፤ ጋዜጣ አዟሪዎችን ወደ ዘብጥያ አስላኳቸው፤ ሌሎች መንግሥታዊ ጋዜጦች በአዲስ ድምጽ ጋዜጣ እንዳይደፈጠጡ በመስጋታቸው።
ጳውሎስም “ሚኒስትሮቻችን ጋዜጣ አዟሪዎቻችንን ማሰር ጀመሩ!” ብሎ በአዲስ ድምጽ ላይ በመጻፉ “የጋዜጣዋ ኅትመት ሥርጭት ተገትቶ ጳውሎስ ከሥራው ተሰናበተ፤ ድፍረቱን እንደ ዝናር እንደ ታጠቀና እንደ መውዜር እንዳነገተ።
ብርሃኑ ዘሪሁንም:- የወሎን ድርቅና ረሃብ በንሥር የሥነ-ጽሑፍ ዓይኖቹ ተመልክቶ፤ ቢሮክራሲያዊ የመንግሥት የአሠራር ድክመትን በብዕሩ ትሩፋት ቃኝቶ፤ “ማዕበል የአብዮቱ ዋዜማ”፣ “ማዕበል የአብዮቱ መባቻ” እና “ማዕበል የአብዮቱ ማግስት” ሲል ሦስት መጻሕፍትን ደጎሰና ለገሰ፤ ለዘመናት ኢትዮጵያን አልለቃት ያለውን ድርቅ በጥዑም በተባ ብዕሩ በጥልቀት እየዳሰሰ።
አጀማመራቸው እንዲህ ነበር። የሀረርጌው-የጋራ ሙለታው-የግራዋው ተወላጅ የዕድሜ ታላቃቸው መዝገቡ አባተ፤ ለአቅመ-ፊደል መቁጠር ሲደርስ፤ እናቱ ወይዘሮ ቦጋለች ወልደጻድቅ የኔታ (ቄስ) ትምህርት ቤት አስገቡት። የኔታ ደግሞ ግእዝና አማርኛ ትምህርት አስተማሩት። ከዚያም ወደ መደበኛ ቀለም ትምህርት ቤት እንዲዋብ (እንዲሄድ) ማረጋገጫ ሰጡት። እርሱም:- “በየኔታ ጉሮሮ ጠጅ ይንቆርቆር በልጆች ጉሮሮ ቀለም ይንቆርቆር!” ብሎ አንድ የፊት ጥርሳቸው ከወለቀው ሕጻናት ጓደኞቹ ጋር የኔታን አመስግኖና መርቆ ወደ ሐረር ከተማ ተጓዘ፤ የተወለደባትን ትንሿ ግራዋ በናፍቆት ዓይኖቹ ዓይቶ እየተከዘ።
ጳውሎስ ኞኞም በመጽሐፍ ቅዱስ 14 መልእክታትን የጻፈው ብርሃናተ-ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ከፍ ያለ ስም የተፀውዖ ስሙ መጠሪያ ሆኖለት፤ “አማረ” የሚለው ቀዳማይ ስሙ ተቀየረ፤ በድሬዳዋ መሠረተ-ክርስቶስ ትምህርት ቤት በመማሩም ለቀጣይ የድርሰትና የጋዜጠኝነት ሥራዎቹ የሚበጅ ጥሩ ስንቅ በድብቁ የአእምሮው ጓዳ እያኖረ።
ብርሃኑ ዘሪሁንም በአባቱ መሪጌታ ዘሪሁን መርሻ እጁን ተይዞ በጎንደር የቤተክህነት ትምህርት በጥልቀት ተምሮ ገና ከማለዳው የጥሩ አዝመራ ድርሰት መዝራት ጀመረ፤ በልጅነት የማሰላሰል አእምሮ ለቀጣይ ድርሰት ሥራዎቹ መንገዶቹን እያሰማመረ።

በጥልቀት አሳቢዎቹና ተመልካቾቹ፣ በሳል አንባቢዎቹና የድርሰቱ ዓለም ስመ-ጥሩዎቹ መዝገቡ አባተ፣ ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘሪሁን፤ በየሥራ ቦታቸው በነበሩበት፤ በ1966ቱ አብዮት ዋዜማ ለውጡ ዘመን አፍላ የትኩሳት ወቅት፤ “እናንተ “ጋዜጠኞችና ደራስያን የንጉሣዊውን ሥርዓት ታሞካሻላችሁ?!” ብለው ሦስት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ሽጉጥ ደግነው ያስፈራሯቸው፤ ግና ፈጣሪ-አምላክ ዕድሜ ሰጥቶ እርሱ እንደ ፈቀደ ያኖራቸውና በሰአቱ የጠራቸው፤ የአንድ ዘመን ደራስያንና ጋዜጠኞች ናቸው፤ የሙያ ፍቅርና የሀገር ፍቅር ያስተሳሰራቸው።
አዎ! መዝገቡ አባተ፣ ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘሪሁን:-ደራሲነትና ጋዜጠኝነት ትልቅ የሕይወት ጉዘት ትምህርት ቤት ሆኖ ያስተማራቸው፤ መጠየቅ ያደርጋል ሊቅ/ልኂቅ” የሚለውን ብሂል እንደ ቀበቶ መታጠቃቸው የሚታወቅላቸው ፤ “ካልጠየቅክ አታገኝም!” (If you don’t ask, you don’t get it) የሚለውን የማኅተመ ጋንዲ አባባል ጎላ አድርገው መናገራቸው የሚጠቀስላቸው የኢትዮጵያ የድርሰቱ ዓለም እሙሮች ናቸው፤ የዛሬውም ሆነ የመጭው ትውልድ የሚያደንቃቸው። አበቃሁ።
ፎቶ በቅደም ተከተል:-መዝገቡ፣ ጳውሎስና ብርሃኑ

መዝገቡ አባተ፣ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘሪሁን:-መጽሐፍ በሊታዎች

Leave a Reply