Cart

Authors

  • Home

Natnael Kerealem

ናትናኤል ቀረዓለም ወርቁ በአርባ ምንጭ ከተማ በ1990ዓ.ም ወርኃ ጥር ላይ ተወለደ፡፡ ለቤተሰቦቹ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ትምህርቱን በአርባ ምንጭ ከተማ ተከታትሏል፡፡ በ2010ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ

Description

ናትናኤል ቀረዓለም ወርቁ በአርባ ምንጭ ከተማ በ1990ዓ.ም ወርኃ ጥር ላይ ተወለደ፡፡ ለቤተሰቦቹ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ትምህርቱን በአርባ ምንጭ ከተማ ተከታትሏል፡፡ በ2010ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅን በመቀላቀል በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን እንዲሁም ከአድማስ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

ናትናኤል የባንኩን ኢንዱስትሪ በመቀላቀል እና ከሀገራችን የግል ባንኮች በአንዱ ውስጥ የዋናው መሥሪያ ቤት ኦዲተር በመሆን እያገለገለ የሚገኝ ቢሆንም በዋናነት የሚታወቀው ግን በተከታታይ ባሳተማቸው እና ለተደራሲያን ባበቃቸው መጻሕፍቱ ነው፡፡

ለሥነ ጽሑፍ እና መጻሕፍት ልዩ ፍቅር እንዳለው በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያወሳው ናትናኤል “የነፍስ ጥሪዬ” ነው ለሚለው ሥነ ጽሑፍ ሁሉ ነገሩን እንዳስገዛ ይናገራል፡፡

ናትናኤል ቀረዓለም ለንባብ ያበቃቸው መጻሕፍት “ዛሬ ቅዳሜ አይደለም” “ትናንት እመጣለሁ” እና “እውነት / አዛምድ” ይሰኛሉ፡፡

የመጀመሪያ የታተመ መጽሐፉ የሆነው “ዛሬ ቅዳሜ አይደለም” በወርኃ ነሐሴ 2015 ዓ.ም ለአንባቢያን የቀረበ ሲሆን በተለያዩ የዘፈቀደ ሀሳቦች እና አጫጭር ታሪኮች የተዋቀረ ሲሆን ለየት ባለ ይዘቱ እና የአጻጻፍ ቴክኒኩ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል፡፡ በመጽሐፉ ፍልስፍና፣ ሥነ መለኮት፣ ሥነ ተፈጥሮ እና ሰዋዊ ስሜቶች በስፋት የሚንጸባረቁበት ሲሆን በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሦስት ጊዜ ሊታተም ከመቻሉም በላይ ለደራሲው አድናቆትን አትርፎለታል፡፡

በወርኃ ነሐሴ 2016 ዓ.ም የታተመው የደራሲው ሁለተኛ መጽሐፍ “ትናንት እመጣለሁ” የተሰኘ ርዕስ ሲኖረው፤ በመጽሐፉ… ሕይወት፣ ተስፋ፣ ጽናት እና ብርታት እጅግ በተለየ መልኩ ከመገለጻቸውም በላይ ድብቁ የአዕምሮ ክፍል ሊገነዘበው እንዳይችል በታመነ ሌላ ድብቅ የአዕምሮ ክፍል ላይ በሚውጠነጠኑ ሀሳቦች ላይ ጭብጡን መስርቷል፡፡ ደራሲው ለጊዜው ያልሰየመው የቴክኒክ ውቅርም ተንጸባርቆበታል፡፡

የደራሲው ሦስተኛ መጽሐፍ “እውነት / አዛምድ” የተሰኘ ሲሆን ይህም መጽሐፍ በወርኃ ነሐሴ 2017 ዓ.ም ለተደራሲያን ደርሷል፡፡ መጽሐፉ ወጥ ረጅም ልብ ወለድ ሲሆን ሰዋዊ ገጽታን ለብሰው እና ሥጋ ነስተው በአካል እንዲንቀሳቀሱ በሆኑ ገጸ ባሕርያቱ ይታወቃል፡፡ ቃል፣ እምነት፣ እውነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ ቅናት እና የመሳሰሉት በሰውኛ እሳቤ የታሪኩ መዘወሪያ እና ዋና ማጠንጠኛ ሆነው ከመጽሐፉ ተገኝተዋል፡፡

ለየት ባለ የአጻጻፍ ቴክኒኩ እና የገጸ ባሕርያት አሳሳሉ የሚታወቀው ደራሲ ናትናኤል ቀረዓለም ከመጻሕፍቶቹ በተጨማሪ በተለያዩ መድረኮች እና ቃለ መጠይቆች ላይ በሚያነሳቸው ሀሳቦች እና የጥያቄ አንኳሮች ከአንባቢያን ልብ ውስጥ ለመግባት የቻለ ወጣት የዘመናችን ደራሲ ነው፡፡

Review

Customer Reviews

Write A Review

AddisBooks Ads