Authors
Description
Kebur Dengay ክቡር ድንጋይ by Yismake Worku
አሁን ይዞልን የቀረበው ክቡር ድንጋይም የዚህ ያዲስ መንገድ ፍለጋው ውጤት ነው፡፡ ይስማዕከ በተፈጥሮ በተለገሰው ክህሎት፣ ሲፈልግ እንዱን ሰከንድ የዘላለምን ያህል ያረዝመዋል፤ ሲያሻው ዘመንን ጠቅልሎ ባንዲት ሰከንድ ውስጥ ይከተዋል፡፡ እንደ ዥረት ፍስስ በሚልለት ቋንቋው ድርና ማግነት ሽምኖ በሚያቀርባቸው ትርክቶች፣ አስጥሞ ትንፋሽን ማስያዝ፣ ከፈለገም እንደ ሜዳ ላይወንዝ በዝግታ ሀሳቦቹን ማፍሰስ ያውቅበታል፡፡ በጠንካራ ብዕሩ የሚያቀርባቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሀገራዊ ሒሶች ድፍረቱን ብቻ አያሳዩም- አስተዋይነቱን ጭምር እንጂ፡፡ በምህረት የለሽ ብዕሩ ጥንቅቅ ያሉ ሀቆችን፤ የማይታበሉ እውነቶችን ስለሚያቀርብ፣ ሀቁ የሸነቆጣቸው፣ እውነቱ የለበለባቸው ለሚያመጡት ጦስ ግድ የለውም፡፡ ስንት ነፍስ እንዳለው ልጠይቀው ከጅሎኝም ያውቃል፡፡ ሆኖም ካለኝ ስስት የተነሳ እንጂ ይህ አይጠየቅም፡፡ ዘመኑን ከሚተርክ እውነተኛ ደራሲ የሚጠበቅ ነውና፡፡ ይስማዕከ ዘመኑን እየተረከ ነው፡፡
በኔ ግምት፤ ክቡር ድንጋይ ምትሀታዊ እውነታ የሚባለው የእጻጻፍ ስልት ልንመድበው የምንችለው የልቦለድ አይነት ነው፡፡ የዚህ ልቦለድ ዋና ገጸ ባህርይ የሆነው ውሻው ተራ ውሻ አይደለም፡፡ ባንድ ወቅት የተከበረ ሰው የነበረ ነው፡፡ ዲዲሞስ ዶሬ፣ ከእለታት ባንድ ቀን በሰውነቱ ላይ አስማታዊ ውላጤ ይከስታል፡፡ ይህ ለውጥ የፈጠረለትን አጋጣሚ ተጠቅሞ የማህበረሰቡን ገመና ይበረብራል፡፡ እንደገና ወደ ሰውነት መመለሻው አስማት ጠፍቶበት ሲዳክር፣ በሰውነቱ ዘመን ያላስተዋለው እውቀት ይገለጥለታል፤ የተጋረደበት ጉድ ባዲስ ህልውናው ይፍረጠረጣል፡፡
በክቡር ድንጋይ ውስጥ ይስማዕከ ያበረከተው ሌላው አዲስ ስልት የከተሞችን ታሪክ ከልቦለዱ ትልም ጋር ማሰናሰል መቻሉ ነው፡፡ ለይስማዕከ ከተሞች ቦታ ሳይሆኑ ራሳቸውን የቻሉ ገጸ ባህርያት ናቸው፡፡ ከላይ ከላይ ከሚታየው ደብዛዛ ገጽታቸው በስተጀርባ ደማቅ ታሪክ እንዳላቸው ያሳየናል፡፡ በበኩሌ፣ የይስማዕከ ዋናው ገጸ ባህርይበዝዋይ እስኪያልፍ ድረስ ዝዋይ ይሄን የመሰለ ትንግርተኛ ታሪክባለቤት እንደ ሆነች አላውቅም ነበር። ታድያ ታሪኩን ሲተርክ፣ የጉዞ ማስታወሻውን እንደሚናዘዝ መንገደኛ ሳይሆን፤ ከጭብጡ ጋርየሚሄዱ ገጠመኖችን ብቻ መርጦ ከዋናው የታሪክ ጋር እንዲጣጣም አድርጎ ነው፡፡ ይስማዕከ በሌሎች ቀዳሚ ልቦለዶቹ ሲያደርገው እንደነበረው፤ ከትረካው መሀል ቆም እያለ፣ ያሰላስላል፣ ይተክዛል፣ ይተርባል፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ትልልቅ ሐሳቦቸንያወጣ ያወርዳል፡፡ በዚህ ልቦለድ ውስጥ ሙሉ ኃይሉን አሰባስቦ የዘመተበት ጭብጥ የሰብአዊነት መንጠፍ ይመስለኛል፡፡ ሰዎች አሰውነት ተርታ ወጥተው ውሻ የሆኑበትን አስደንጋጭ ዓለም አይቶ ያሳየናል፡፡ ከዚህ በላይ አሄድኩ ያንባቢውን ድርሻ መጋፋት ይሆንብኛል፡፡ መልካም ንባብ!
ዶ/ር አድማሱ መሸሻ
Reviews (0)
You must be logged in to post a review.
May you like





Reviews
There are no reviews yet.