Cart

  • Home
  • Fiction

በፍም እሳት ማቃመስ በ ያዕቆብ ብርሃኑ

$20.00

“በፍም እሳት ማቃመስ” Initiating by fire በደራሲ ያዕቆብ ብርሃኑ.

Addis Books!

November 15, 2023 Amharic 174 pages

Authors

Meet the Author

Yacob Berhanu

Books By Yacob Berhanu View All
በፍም እሳት ማቃመስ በ ያዕቆብ ብርሃኑ
በፍም እሳት ማቃመስ በ ያዕቆብ ብርሃኑ
የመሻገር ሲቃ ከዐውሎ ነፋስ ጋር መደነስ በያዕቆብ ብርሃኑ
የመሻገር ሲቃ ከዐውሎ ነፋስ ጋር መደነስ በያዕቆብ ብርሃኑ

Description

በፍም እሳት ማቃመስ በ ያዕቆብ ብርሃኑ
“በፍም እሳት ማቃመስ” Initiating by fire በደራሲ ያዕቆብ ብርሃኑ የተጻፈና በቅርቡ ለንባብ የበቃ አዲስ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የሰውን ልጅ ታሪክ እና ስልጣኔ ከእሳት ግኝት ጋር በማገናኘት በጥልቅ ፍልስፍናዊ እይታ ይተነትናል።
የሰውን ልጅ ከተራ አውሬነት ጎራ ነጥሎ ወደ መለኮታዊነት ያሸጋገረው እሳትን መፈልሰፉ ነበር፡፡ እሳትን ከማላመዱ በፊት የሰው ልጅ ከ20 በማይበልጡ ትንንሽ ቡድናት የሚንቀሳቀስ፣ የአዳኝ አራዊት ሰለባነትን ሽሽት የእውርድንብር የሚቃትት ድንጉጥ ፍጥረት ሆኖ አሳለፈ፡፡ እሳትን ማላመዱ ግን በአንድ ጊዜ ድርድርብ መሳሪያዎችን እንደመታጠቅ ሆነለት፡፡ አብስሎ መብላት ተቻለው፤ ጤናው ተሻሻለ፡፡ ምግቡም በረከተ፡፡ በአንድ ጊዜ ‹food chain›ኑ አናት ላይ ለመቀመጥ በቃ፡፡ እሳቱ ራሱን ከቅዝቃዜና ከአራዊት ጥቃት ለመከላከል እንደ ሁነኛ መሳሪያ አገለገለው፡፡
በእርግጥም የሰው ልጅ እሳቱን እስኪፈለስፍ ድረስ ለመጥፋት የተቃረበ፣ በስራ ፈትነት የሚንጀባረር ለአደጋ የተጋለጠ እንሰሳ ነበር፡፡ (Man was a meandering and jabbering around beast until he discover fire…) እሳትን ካላመደ በኋላ የሰው ልጅ ለስልጣኔው -ም-ት-ክ-የ-ለ-ሽ- መሠረቶች የሆኑትን የእሳት ግኝቶች -ምድጃን (hearth) -መሰዊያን (Altar) እና ማቅለጫን (forge) ፈለሰፈ፡፡
ምድጃው ሁለተናዊ ደኅንነት እና መረጋጋትን አቀዳጀው፡፡ ምድጃው እንደ ‹ሴል› (cell) ሆኖ የሰው ልጅ በዙሪያው እንዲሰባሰብ ምክንያት ሆነ፡፡ ቤተሰብ እንዲመሰረት አገዘው፡፡ ከቤተሰብ አስር ሃያ እያለ ወደ ትንንሽ ማኅበረብነት አደገ፡፡ መረጋጋት ቻለ፡፡ ቀስበቀስ መንደሮችን መገንባት ጀመረ፡፡ በምድጃው ዙሪያ ብዙ ዓይነት ተረቶችን አደራ፡፡ የሰው ልጅ ተረቶች፣ ታሪኮች፣ ሚቶች በሙሉ የመነጩት ከምድጃው ነበር፡፡ ተረቶቹ አፈታሪኮቹ ምናቡን ለመሳል ጠቀሙት፡፡
መሰዊያው መንፈሳዊ በጎነትን አጎናጸፈው፡፡ የዓለም ኃይማኖቶች በሙሉ የመነጩት ከመሰዊያው ነበር፡፡
ማቅለጫው ቅኝቱ የፈጠራ ሆነ፡፡ ከጦር አንካሴና ማጭድ ጀምሮ እስከ ሮኬት ሳይንስ ዛሬም ድረስ እየተራቀቀ ለቀጠለው ቴክኖሎጂያዊ መራቀቁ መነሻው እሱ ማቅለጫው ነበር፡፡ነገርግን በግሪክና መሰል ጥንታዊ ተረታዊ ትርክቶች እንደሚባለው የሰው ልጅ እሳትን ከአማልክት አልሰረቀም፡፡ የሰው ልጅ በመጀመሪያ እሳትን የከዋክብቱ ገጽ ላይ ተጽፎ አየው፡፡ ጫረውም… እሳትን ከክዋክብት ገጽ ለመጫር ደግሞ ከገል እና ኩበት ይልቅ ምናብ ያስፈልጋል፡፡ምናብ ምንጊዜም አሸናፊ ያደርጋል፡፡ ጥቂትስ ስንኳ የተሳሉ ምናቦችን ከመካከሉ መፍጠር የሆነለት ሕዝብ ምንጊዜም የትርክት የበላይነትን ይቀዳጃል፡፡
ስለምናብ ሳወራ ስለድርሰት ብቻ እየተናገርሁ የሚመስለው ካለ መቸስ ምን እላለሁ፡፡ ነገርግን ቴሌስኮፕ፣ ማይክሮስኮፕ፣ የማተሚያ ማሽን፣ ኢንተርኔት፣ ፌስቡክን ጨምሮ በጠቅላላው የኤሮፓ ሥልጣኔ ግኝቶች የምናብ ውጤቶች መሆናቸው እሙን ነው፡፡
የእሳትንም ያህል ፍጹም ቅን፣ ገር እና በስነተፈጥሮው ቀጥተኛ ነገር መኖሩን አላውቅም፡፡ እሳት ከብሉያት፣ ነብያት፣ ወንጌላዊያን፣ ከአፈታሪኮች እና ባለቅንያት ዘመን ጀምሮ ብዙ የተባለለት መለኮት አከል ረቂቅ ክንውን ነበር፡፡ እሳት ሲፈጅ፣ ሲበላ እንጂ ሲያርፍ ማደሪያው የት፣ ሲግለበለብ መከሰቻው ከወዴት እንደሆንስ ስንኳ የሚያውቅም የለም፡፡ እሳት ስሪቱ የነበልባል፣ የፍላጻ ብቻ አይደለም፡፡ የቃል፣ የቀለም፣ የመንፈስ ልዩ ልዩ ዓይነት አለው፡፡ እሳት ንጹህ ነው፤ ቅን ነው፤ ገር ነው፡፡ ግን ደግሞ አውዳሚ፣ ጨራሽ፣ ፈጅ፣ ቀሳፊ፣ ቁጡም ነው፡፡ የዚህ ረቂቅ የነበልባል ቅኝት ጥሪ እና ምሪት ሰብዓዊነትን ማበልጸግ መሆኑ ጥንት ከአፈታሪክ ከነፕሮሚተስ ዘመን ጀምሮ ይታወቃል፡፡
አሳት ሥሪቱ የእንከንየለሽነት፣ የምኅረትየለሽነት መሆኑም እሙን ነው፡፡ እሳት በመንፈሳዊውም (spirited) ይሁን በገቢራዊ (empirical) ባህሪው የሚያሻግር (fire of transmuting) እና የሚያሳርር (fire of destruction) መንታ ጉልበት ያለው ረቂቅ ሁነት ነው፡፡ እሳት የነካውን ሁሉ የሚያነጻ (purifying) ወይም የሚያገረጣ (terrifying) አቅም አለው፡፡ ቁም ነገሩ ለየትኛው አሰልጥነሽዋል/ አሰልጥነኸዋል የሚለው ብቻ ነው፡፡
ቀደም ብዬ እንዳልኩት የሰው ልጅ በመጀመሪያ እሳትን የከዋክብቱ ገጽ ላይ ተጽፎ አየው፡፡ ያም በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈ – ምልክት ሆነለት – … ነብዩ ኢሳያስ ለነብይነት የተመረጠበትን አኳኋን በሚናገርበት በትንቢተ ኢሳያስ ምዕ 6፡8 ላይ እንደምን በፍም እሳት መቃመስን ተቃምሶ መንጻትን እንደተቀዳጀ ሲገልጽ…
‹‹ከሱራፌል አንዱ ወደ እኔ ተላከ፡፡ በእጁም ከመሰዊያው በጉጠት የወሰደው ፍም ነበረ፡፡ አፌን ዳበሰበትና ‹እነሆ ይህ ከንፈሮችህን ነክቷል፡፡ በደልህም ከአንተ ተወገደ፡፡ ኃጥያትምህም ከአንተ ተሰረየልህ› አለኝ፡፡›› ይላል፡፡
የሰው ልጅም የእሳት አቀባበል እንዲህ ይመስለኛል፡፡ ልክ የባላገር እናት የአራስ ቤት ጨቅላ ልጇን ወደ ሕይወት ለመጥራት በቅቤ እንደምታቃምስ እንዲያ የሰው ልጅ የነቢይ በሆነ በእሳት መቃመስን ተቃመሰ፡፡ ከእሳት ጋር መገናኘቱ ሁለንተናውን የሚያሻግር ክስተት ሆነለት፡፡ መቼ? የት? የሰው ልጅ ከእሳት ጋር ተዋወቀ ሳይንስ ባዝኖ ባዝኖ መልስ ቁርጥ ያለ መልስ ያጣላቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በደፈናው እስከ 2 ሚሊዮን ዓመታት ይገመታል ብሎ ማለፍ ይሻል ይመስለኛል፡፡ ነገርግንስ የሰው ልጅ እሳቱን ማላመዱ፣ በትንታግ መፈተኑ፣ ነበልባሉን መግራቱ ራሱ የሰው ልጅ ብዙ ዓይነት ሞራላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሥነልቦናዊና አካላዊ ሽግግር እንዲያከናውን ረዳው፡፡
እሳትን ከፈለሰፉት የመጀመሪያዎቹ አውሬ መሰል የሰው ልጆች እስከ እሳትን ወደ ኤሌክትሪክ የቀሩት ድረስ ከ50 – 60 ሺህ ትውልዶች እንደተፈራረቁ ይገመታል፡፡ የእኛ ግን እርግማን ይመስላል፡፡ ሌላው ዓለም እሳቱን ከአመድነት ወደ ስማርት ምድጃነት ከፍታ ሲያሻግር እኛ ዛሬም ጉልቻዋን የሙጥኝ ብለናታል፡፡ ከጥንታዊነት (primitive sentiment) ያልተሻሻለ ቢሆንስ ስንኳ… ለዘመናት ጉልቻውን ታክከን ተረቱን ማንዘገጋችን አልቀረም፡፡ መሰዊያዎችንም (የአምልኮ ቦታዎች) በዓይነት እና በጥራት እየገነባን ስናደገድግ ምዕታት አልፈዋል፡፡ ለሰብዓዊ ልማት ከፍተኛ ጠቀሜታ የነበረውን ዋነኛውን የእሳት ግኝት ማቅለጫውን (forge) ግን ሆነ ብለን ረሳን፡፡ ማቅለጫውን ሙሉ ለሙሉ ብንረሳ ከብዙ መቶ ሺህ ዓመታት በፊት የመጀመሪያው የሰው ልጅ በተጠቀመበት ጦር ጀት የታጠቀውን ጣሊያንን ለመግጠም ተገደድን፡፡
የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ታሪክ በተለይ ከአክሱም ውድቀት በኋላ የነበረውን ሂደት በጥልቀት የሚመረምር ሰው የጎደለን ነገር ማቅለጫው እንደነበር ግልጽ ይሆንለታል፡፡ ማቅለጫው ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ፣ ሌላም ሌላም ብዙ ነገር ነው፡፡ በዚህ መጽሐፌ ከተካተቱ አስራ አንድ መጣጥፎች ውስጥ ስድሳ ገጾችን በሚሸፍነው የመጀመሪያው ክፍል የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የጎደለው የመሰለኝን የማቅለጫውን ነገር በጥድፊያም ቢሆን ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ፡፡ ሌሎች በዚህ መጽሐፍ ስር የተካተቱ ሌሎች አስሩም መጣጥፎቼ በልህቀት ለሚያነባቸው የእሳት ንክኪ እንዳላቸው አምናለሁ፡፡

Reviews

There are no reviews yet.

Be the first to review “በፍም እሳት ማቃመስ በ ያዕቆብ ብርሃኑ”