Description
ዋናተኛ ፀሐይ By Elssa Mulugeta
የአልሳ ሙሉጌታ ሁለተኛ መፅሐፍ የሆነውን ‘ዋናተኛ ፀሐይ’ን በትኩሰነቷ ፉት አደረኳት። ኤልሳ ከፌስቡክ ትውልድ ፀሐፊያን አንዷ ነች። ከዚህ ቀደም ‘ሐምራዊ ተረኮች’ የተሰኘ የአጭር ልብወለዶች ስብስብ አስነብባን ነበረ።
ዋናተኛ ፀሐይ የስድስት አጫጭር ታሪኮች ስብስብ ነው። እነዚህ ታሪኮች ‘ከአኒያኑ (ዋናተኛ ፀሐይ)’ እና ‘ሌባ ሻይ’ ውጪ ያሉት በተለመዱ የአጭር ታሪኮች አፃፃፍ የተፃፉ ሲሆን፣ ከአኒያኑ (ዋናተኛ ፀሐይ) ‘ፋንታሲ’ ቀመስ ሲሆን፣ ‘ሌባ ሻይ’ ደግሞ ታሪክ ቀመስ የፈጠራ አጭር ታሪክ ነው።
(ኤልሳ ፋንታሲ ታሪኮችን ስትፅፍ ጎበዝ ነች። የመጀመሪያ መፅሐፏ ላይ በደንብ አሳይታናለች። ይህን አፃፃፍ አሳድጋው ሙሉ ለሙሉ ፋንታሲ ልብወለድ ብትፅፍ ብዬ እመኛለሁ።)
ከስድስቱ ታሪኮች ውስጥ አምስቱ ታሪኮች ዋናው ገፀ ባህሪያት ሴቶች ናቸው። ‘ዜማና ሰውነት’ የሚለው በከፊል ሴት ነች። ስለዚህ ሙሉ ታሪኮቹ ዋና ገፀ ባህሪያቱ ሴቶች ናቸው ብንል ስህተት አይሆንም።
እነዚህ ሴት ገፀ ባህሪያት አንድ ነገር ያመሳስላቸዋል። መከራ ገፊ ናቸው። ችግር እያሳደደ የሚደቃቸው ናቸው። ከደስታቸው ይልቅ ፍዳቸው በየገፁ የሚነበብ።
አባቷ ወንዝ እየተከተለ የተዋት ታዳጊ፣ ጎረምሶች በህብረት የደፈሯት የዩንቨርስቲ ተማሪ፣ ቤተሰቦቿ የጣሏት ጨቅላ፣ ቤተሰቦቿ ያልተቀበሏት ሴት፣ ከእድሜ ጋር ትግል የገባች እንስት፣ በሁለት ወደጆቿ የምትቃኝ ተፈቃሪ ሴት…
ለደራሲዋ ይህ መፅሐፍ መከራ በዛበት የሚል ጥያቄ አቅርቤላት ነበረ። ”ሐዘን አዝለን አይደል እንዴ የምንኖረው?” በማለት ጥያቄዬን በጥያቄ መልሳልኛለች።
እውነት ነው። ዘመኑ የመከራ ነው። ይብዛም ይነስም ሁላችንም መከራ አለብን። በየቀኑ የሴቶች መደፈር፣ ግድያ፣ ድብደባ መስማት ብርቃችን አይደለም። የጦርነትና የችጋር ዜናዎች ለጆሯችን ባዳ መሆን ከአቆሙ ከራርመዋል። ልጅ ወልዶ የሚረሳ ወላጅ እልፍ ነው። በዚህ ዘመን መከራን እንደ ጭብጥ ይዛ የምትነሳ ደራሲ ዘይዳለች ማለት እንችላለን።
Reviews (0)
You must be logged in to post a review.




Reviews
There are no reviews yet.